NES Commentary 47 in Amharic

ባንትይሁን ትእዛዙ, M.Eng., P.Eng., PMP, Electrical Engineering, University of Toronto, Canada Founder 4EPR Enterprise, (www.4epr.org)

ፈቃዱ ፉላስ, RPh, PhD Research Preceptor; Clinical Pharmacist. UnityPoint Health, St. Luke’s Regional Medical Center, Sioux City, Iowa, USA (newsletter.p2pbridge.org)

ማሞ ሙጨ, DST/NRF Research Professor on Science, Technology and Innovation, Faculty of Engineering , Tshwane University of Technology, Pretoria, South Africa (www.sarchi.org)

ረቂቅ ጠቅላላ ሓሳብ፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትንና ጉዳትን ለማቆም፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በጤና በኢኮኖሚና በህብረተሰብ ህልውና ላይ ለማድረሰ የተደገነውን ቃታ አዙረን ወደ በመመከት፤ ወደ አጥቂነት፤ ከህመሙ ነፃ የሆነ ሁኔታ ተቀዳጅቶ በኢኮኖሚውም እምርታዊ እድገት ለማምጣት የሚያስችሉ ሶስት አቢይ ተግባሮች ቀርበዋል። እነዚህም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሰረቱ እርምጃዎች፡ (ሀ)ህዝብን በስፋት ያሳተፈ እንቅስቃሴ የወረርሽኙን መሰራጨት ያቆማል ህብረተሰቡን ለልማት ያዘጋጃል፤ (ለ) በገጠሩና በከተሞች ለሚኖሩት ሰዎች ላካባቢያቸው ተስማሚ የሆኑ የህዝብ
ተሳትፎ ማሳኪያ ዘዴዎችን መተግበር ውጤቱን ዘላቂ ማድረግ ይቻላል፤ (ሐ)በቁጥር ከፍተኛ የሆነውን ወጣት ተግባራዊ የእውቀት መገብያ ሥራዎች ላይ በማሰማራት ተግባራው ልምድ እያገኘ ሃላፊነትን በመረከብ አገር በምትፈልጋቸው የሥራና የምርት መስኮች እንዲሰማራ ያደርጋል።

፩፡ መንደርደሪያ
ውድ ወገኖቻችን ሆይ፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ትንሽ ትልቅ፤ ደሃ ሓብታም፤ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጄኔራል ልዑል፤ አዋቂ መሃይም፤ ልጅ ሕፃን አዛውንት ሳይል ሁሉንም የሰው ልጅ የተፈታተነ አደጋ አገራችን ውስጥ አንዣቧል። የዓለም አገሮችን ሁሉ አንዳቸውም ለእንዲህ ዓይነት ጥቃት ሳይዘጋጁ የመጣ ዱብዳ ነው። በሃብታቸው በሳይንቲስቶቻቸው በሃይላቸ የሚመኩ አገራትን ሳይቀር ያንበረከከ አደጋ ነው። ኢትዮጵያን ፈጣሪ እንደገና ሸፋፍኖ ብልሃቱን ዘዴውን ስጥቶን በአንድ ላይ ከአደጋው እንድንዘልቅ የሁሉም ሰው ምርምር ትጋት ጸሎትና ምኞት ነው። እኛም በጥናታችን የቀመርናቸውን ብልሃቶች አብረን እየተመካከርን እንድንተገብር ይህን መተግብሪያ አቅርበናል።


ሁሉም እንደሚቀናው እንደሚሳካለት፤ በፀሎት በትጋት በሓብት በእውቀት በርህራሄ በመረዳዳት በመተሳሰብ፤ ፈጣሪ አድባር በምናመልክበት፤ በሳይንሱ በዕውቀቱ ሁሉ እንተባበር፤ ሴት ወንድ ባልቴት ሽማግሌ ወጣት፤ ገብሬ ነጋዴ ሰራተኛ አሰሪ ወንጀለኛ ዳኛ ተማሪ አስተማሪ መንግስት ህዝብ ባንድ ላይ ከመዓቱ እንዲሸፍነን እንትጋ። ለአድዋ ጦርነት ድል ለህልውናቸው መከበር፤ በኛ አምሳልም በቅኛ አገዛዝ ወድቀው የነበሩት ሁሉ ተስፋና ወኔ ጥንካሬ ገንብተው የተዋጉትና ነፃነታቸውን የተቀዳጁት፤ እግዚአብሄር ፈጣሪ አምላክ አላህ ብለው ለነገ ሳይሉ በመሰለፋቸው ነበር። ከ124 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን የፈተነና ድል ያጎናፀፈ አምላክ አሁንም እንዲረዳን፤ ቂም በቀል ትተን እንትጋ። ወንድሞች እህቶች እናቶች አባቶች በዚህች ጊዜ ተባብረን ያለቀውስ ያለዕልቂት በትጋታችንና በዕምነታችን ጸንተን ከዚህ አደጋ ያለብዙ ጉዳት ብንሻገር

ለልጅ ልጆቻችን ሌላ አራያና ምሳሌ ትተን እናልፋለን። ለዚህም እንዲቀናን በምክክርና አካባቢያችሁ ያለውን ሁኔታ አመሳክሮ ለመተግበር እንዲያመች ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ብልሃቶችን ከነምክንያታቸው፤ ከነ አሰራራቸውና የሌሎችንም ተመክሮዎች በመጨመር ባጭሩ አቅርበናል።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዝቅተኛ ደረጃ ስለሆነ ሃብታም አገሮች የሚወስዱትን እርምጃ የመውሰድ አቅሟ ውስን ነው። ሃብታም አገሮች ህዝቡ ሥራውን እንዲዘጋ ተደርጎ፤ እራሳችሁን አግልላችሁ ተቀመጡ ብለው ያዘዙት ለሰራተኞችና ለትቅዋማት መደጎሚያ በቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላር የማፍሰስ አቅሙ ስላላቸው ነው። ሰዎች እራሳቸውን አግልለው እቤታቸው ቢቀመጡ ከሰው ወደሰው በመነካካት የሚተላለፈውን ቫይረስ መሰራጨቱን የሚገታና ነፍስ የሚያድን መሆኑ የተረጋገጥ ቢሆንም ሥራ ላጡት ማቆያ ሃብት ለሌለው አገር አዳጋች ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሃብታም አገሮች የስራ መስኮችን ዘግታ ሰዎች እቤታቸው እንዲቆዩ ማስገደድ የሚያመጣው ጉዳት በሽታው ከሚያስከትለው ጋር ሲወዳደር ሊበልጥ ስለሚችል ሰፊ ጥንቃቄ ያስፍልገዋል ውይም የተለየ አማራጭ መወሰድን ይሻል። ለኢትዮጵያ ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ አበይት ዘዴዎችን ከሁለት የውጭ አገሮች ተመክሮዎች ጋር አብረን በማቅረብ፤ የቫይረሱን መሰራጨት ለማቆም ከሃብታም አገሮች ዓይነት አዋጅ የተሻለ ህዝባዊ ዘዴን እናሳያለን።

፪: የቫይረሱ ምንነት


ኮቪድ-19 ቫይረስ በመተንፈሻ (አፍንጫና አፍ) እና ዓይን ገብቶ ከጉረሮ ጀምሮ ሳምባ ስይቀር የመተንፍሻ አካልን በመጉዳት ትንፋሽ በማሳጣት የሚገል በሽታ ነው። የአየር መተላለፊያ እየቆሰለና እየጠበበ ሲሄድ መጀመሪያ የሚጠቁት ሌላ ህመም ያለባቸው፤ የሰውነት አካላቸው ደካማ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ይህ የሆነበት ምክንያት ሰው አንድ አደጋ ወይም ቁስል በሚያገኘው ጊዜ የሚያድኑት እደም ውስጥ ባሉት የነጭ ደም ህዋሳት ጥገና ነው። እነዚህ ጠጋኝ የደም ህዋሳት ሌሎችም የደም ይዘቶች ህመም ያለበትን ሰው እየረዱ ባለበት ወቅት ሌላ ቫይረስ ሲገጥማቸው ወደዚያ በሚሄዱበት ጊዜ የደካማው ሰው መከላከያ ስለሚያንስ ነው። ይሁንና ኮቪድ-19 እታች እንደሚታየው የተበከሉት ሰዎች ቫይረሱ በአካል ውስጥ እስክሚያድግ ስለማይታወቅ ጉዳቱ ምንም ማስታገሻ እዲወሰድ ሳይቻል ከፍተኛ የውስጥ ቁስለት ላይ ይደርሳል። በመሆኑም ለደከመ ሰው ብቻ ሳይሆን ጤነኛ ወጣትንም በአስፈሪ ደረጃ እያጠቃ ይገኛል። ቫይረሱ በዕቃ ወይም በእጅ ላይ ካረፈ፤ አረፈበት ቦታ ስለሚጣበቅ በሳሙና ፈትጎ መታጠብ ወይም ባልኮል ካልሆነ በቀላሉ አይለቅም።


የኮቭድ-19 ህመም ምልክቶች – (፩)ትኩሳት (፪) ደረቅ ሳል (ሐ) የጥንቻ ህመም (መ) መተንፈስ መቸገር (ሠ) የደረት ውጋት (መ) የድንዛዜ ስሜት ይገኙባቸዋል። በአብዛኛው ከጉንፋንና ከኢንፍሎንዛ ስለማይለይ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ነወ።

፫: ኮቪድ-19 ቫይረስ እንዴት ይሰራጫል

 1. ኮሮና ቫይረስ በዋናው የሚተላለፈው ከሰው ወደሰው ነው። በቫይረሱ የተበከለ ሰው ሲስልና ሲያነጠስ ባፉና ባፍንጫው የሚወጣው ፈሳሽ ኮቪድ-19 ቫይረስን ስለያዘ አካባቢውን ይበክላል። ቫይረሱ ብዙ ጊዜ አየር ላይ መቆየት ስለማይችል የታመመው ሰው እጆች፤ ሌሎች አካላቶች፤ ልብሶች፤ ዕቃዎⶭ እንዲሁም ቅርብ ያለ ሰው ላይ ያርፋሉ። ቅርብ ያለው ሰው በቂ መከላከያ ያላደረገ ከሆነ ወዲያውኑ ቫይረሱ የመያዝ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። የታመመው ሲስል ሲያነጥስ ያልነበሩ ሰዎች ደግም የታመመው ሰው በቫይረሱ የበከላቸውን ነገሮች በመንካት ቫይረሱን ይወስዳሉ።
 2. ኮቪድ-19 ቫይረስ የያዘው ሰው እስክ 14 ቀናት የቫይረሱን መኖር ስለማያሳይና ስለማያሳውቅ ከእስትንፍሱ በሚወጡትና በእጆቹ ቫይረሱን ስለሚያስተላልፍ ብዙ ሰዎች ሳያውቁት ሊበክሉ ይችላሉ።
 3. ከዚህ በተጨማሪ ቫይረሱ የያዘው ሰው የቫይረሱን ምልክት ቢያሳይም ባያሳይም ወደሌላ ማስተላለፍ ስለሚችል የቫይረሱን መሰራጨት መቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ ነው።
 4. ሆኖም ቫይረሱ የያዘው ሰው ለ14 ቀናት ህመሙ ዕድገት ካላሳየ የሰውነቱ የደም ጠጋኞች ቫይረሱን በማጥፋት አድነውታል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ማሰራጨት አይችልም ተብሏል።

፬፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ

 1. ላለፉት ስድስት ሳምንታት በትጋትና ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የቫይረሱ ስርጨት እንዲታገትና ጉዳቱም ትንሽ እንዲሆን ላደረጉት ሁሉ ከፍተኛ ያክብሮት አድናቆት እየገልጽን ለሚቀጥሉት ሂደቶች የተሻሉና ለኢትዮጵያ ሁኔታ የበለጠ ውጤት ያስገኛሉ የምንላቸውን አቅርበናል።
 2. ከመቶ አስር ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ዘጠና ሚሊዮኑ ተበታትነው በሚገኙ የገጠር መንደሮችና ሰፈሮች ይኖራል
 3. ቀሪው ሃያ ሚሊዮን ደግሞ ትናንሽና ትላልቅ ከተማዎች ውስጥ ይኖራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ነገሮች ባለመሟላታቸው፤ የአሰራር ዘዴ ባለመዳበሩ፤ የአገር ኢኮኖሚ ባለመዳበሩ የሰዎች ገቢ አናሳ ነው።
 4. ከተማዎች ከሚኖረው ሃያ ሚሊዮን አስራ አምስት ሚሊዮኑ በዕየለቱ በሚሰራው ስለሚተዳደር አብዛኛው ከጥቂት ቀናት በላይ ያለስራ እቤቱ ቢቀመጥ ወደ ችግር የሚጎዳ በመሆኑ ውሳኔ ላይ ግምት እንዲሰጠው ያስፈልጋል።
 5. መንግስት ከአብዛኛው ህዝብ በቂ ታክስ ስለማይሰበስብ፤ የህዝቡም የገቢ አቅም ለአገልግሎት ሰጪ የግል ተቅዋማት ውጤታማ በሆነ መንገድ አዋጪ አገልግሎት ለመስጠት የሚያበቃ ሁኔታ ስለሌለ የህክምና አገልግሎት ሰጪዎች አናሳ ነው።
 6. ሰባ ሚልዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ወጣትና አፍለኛ ኃይል ዕውቀት በማዳበርና ምርትን በማጎልበት ተሰማርቶ አገሩን ለመገንባት በጉጉት የሚገኝበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ እቤትህ ተቀመጥ ብሎ ማገዱ ጉዳቱ ስለሚልቅ የተለየ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

፭፡ የኢትዮጵያ ሁኔታና ኮቪድን ለመከላከል መደረግ የሚችሉ አማርጮች

፭-ሀ፡ በከተማዎች ለህዝብ መድረስ


አሁን እየተደረገ ያለው መተሳሰብ፤ መረዳዳት፤ ያለውን ማካፈል / ማዕድን ማካፈል እጅግ በጣም ወደር የሌለው የሰውነትን ማንነትና እውነተኛ ገጽታ የሚሳድግ ነው። በተለይም አዲስ አበባ እየተደረገ ያለው በጎ ሥራ ከተስፋፋ የወገንን ጤንነት ከመታደግ አልፎ ከፍተኛ መተማመን የሚፈጥርና ለዘላቂ ልማት ሕዝብ የሚያስተባብር አርአያነት ነው።
ይህን ጽሁፍ ስናዘጋጅ በአዲስ አበባ በባሕር ዳርና በሌሎችም ከተሞች አቅም የሌላቸውን የህዝብ ክፍሎች ለመርዳት እየተደረጉ ያሉ እርምጃዎች

 1. ከሺህ በላይ የሚሆኑ ምግብ ማሰራጫዎችን ዘርግቶ በደህናው ጊዜ ምግብ ያገኙ የነበሩና አሁን የተቋረጠባቸውን እየተደረሰላቸው መሆኑ ግሩም ነው።
 2. ከቤታቸው ሆነው ችግር ላይ ይወድቃሉ ብሎ በመስጋት የጤና ባለሙያዎች ከቤት እቤት እየተዘዋወሩ ለመድረስ እየተዘጋጁ መሆናቸው
 3. ማዕድ ማጋራት የተባለውን አነሳሽነት በመከተል፤ በሥራቸው መቋረጥ የቤት ኪራይ መክፈል ላቃታቸው ተከራዮች አከራዮች የጥቂት ወራቶችን እንዳያስከፍሏቸው ለተደረገው ጥሪ አከራዮች እያደረጉ ያሉት መልካም ተግባር የህዝቡን ርህራሄና መተጋገዝን ያሳያል። በዚህም ዓይነት ወጣቶች ህዝብን እጅ በማስታጠብ ቫይረስን ለማስወገድ የተደረገና ሌሎችም ህዝብ ለህዝብ እየተደረጉ ያሉ የመተጋገዝ ተግባሮች እጅግ በጣም አኩሪና የሚያነቃቁ ናቸው።

በነዚህ ላይ አክለን የምናቀርበው

 1. በሽታው ከውጭ እንደጀመረ ይታወቃል፤ ይህንን ሁኔታ ሕዝቡ ዘንድ ተደብቆ ባልታሰበ መንገድ እንዳይሰራጭ ሰውን ሃላፊነት ስጥቶ አካባቢው በቫይረሱ ሊበከሉ የሚችሉትን ሰዎች ተከታትሎ አስፈላጊው መገለል እንዲያደርጉና ወደ ሌሎች እንዳያሳልፉ ሃላፈነትን ማስጨበጥ።
 2. ሌሎችም የቫይረሱ ስሜት ያላቸው ለአካባቢው የህዝብ ተወካይ እንዲታወቁ በማድረግ ስርጭቱን ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር እንዳይተላለፍ መገደብ።
 3. ይህን ለማድረግ እድሮች፤ ማህበሮች፤ የዕምነት ክምችቶች፤ መንደሮች፤ ቀበሌዎች አባላቶቻቸውን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ያለ አቅማቸውን በማዳበር ባጭር ወጭና ጊዜ ነጻ ህብረተሰብ ሆኖ እንዲቀጥል ይሁን።
 4. የእነዚህ የአካባቢዎች ተወካይ ከከትማ አቀፍ ተመሳሳይ ማህበሮች ጋር በመተባበርና ከከተማ አስተዳደሩና ከአገር አቀፍ የወረርሽኝ መምሪያው የሚሰጠውን መመሪያ መተግበር ተመክሮዎችን መለዋወጥ።
 5. በያመቱ ከገጠሮች አዲስ አበባ የሚገባው ከሁለት መቶሺህ ያላነሰ ህዝብ በደህናው ጊዜ እንኳን ከተማዋን በአስተማማኝ ቀጣይ አገልግሎት እየሰጡ ማስተዳደር ፈታኝ ነው። እንደ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያለ አደጋ ሲመጣ ቤት ለሌላቸው ለመንገድ አዳሪዎች ለሥራ አጦች ከፍተኛ ጥቃት የደርሳል። ይህንን በእንደዚህ ዓይነቱ ጊዜ አጢነን፤ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነው ነባር ከተማዎችን ማስተንፈሻ የሚሆኑ አዳዲስ ከተሞችን መግባት ወሳኝ ሃሳብ እንደሆነ እንወጥን።

፭-ለ፡ በገጠር ኢትዮጵያ ለህዝብ መድረስ ማሳተፍ

 1. በብዙሃን የመገናኛ ተቅዋማት እንደተገለጸው አንዳንድ ክልሎች የገጠሩን ሕዝብ ከኮሮና ለመጠበቅ በወረዳ፤ በምክትል ወርዳና በገብሬ ማህበራት አስተዳደሮች በኩል ስለኮቪድ 19 ትምህርታዊ መግለጫ መሰጠቱ ተገልጧል።
 2. እንዚህ ብዙዎቹ የገጠር መንደሮች(ከሰባ በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖርባቸው) የኤሌክትሪክ ሃይል ስለማይደርሳቸው እንደከተማዎቹ መረጃዎቹን በቴሌቪዥን መከታተል አይችሉም፤ አንዳንዶች ደግሞ ሬዲዮን እንኳን ስለሌላቸው ስላገራቸውም ሆነ ስለ ዓለም ሁኔታ የሚሰሙት ከወሬ ወሬ ነው። በመሆኑም ዜናው ዘⷝይቶ ከመድረሱም ሌላ በተከታታይ ለማስተማር አስቸጋሪ ነው።
 3. በገጠሮች ተበታትኖ የሚኖረው ህዝብን በቫይረሱ እንዳይጠቃ ከቫይረሱ ነጻ ያልሆኑ ሰዎችና ዕቃዎች እንዳይደርሱበት ማድረግ። በዚህም ምክንያት ወደ ገጠሮች መግቢያ መንገዶችን መቆጣጠር ስርጭቱን አቅቦ የመንደሮችን ጤና ይጠቃል
 4. የገጠሩ ህዝብ ከተማ እንደሚኖረው ህዝብ ሰፊ ግንኑነቶች ስለሌለው ለቫይረሱ ተጋላጭነቱ ትንሽ ነው
 5. ይህን ለማድረግ ማህበሮች፤ የዕምነት ክምችቶች፤ መንደሮች፤ የገበሬ ማህበሮች አባላቶቻቸውን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ያለ አቅማቸውን በማዳበር ባጭር ወጭና ጊዜ ነጻ ህብረተሰብ ሆኖ እንዲቀጥል ይሁን
 6. እንዲያውም እነዚህ ህብረተሰቦች ግንኙነታቸውን በማሳደግ የጋራ ልማት ፕሮጄክቶችን እየቀረጹ እንዲሰሩና ወደተሻለ ኑሮ እንዲሸጋገሩ ይጠቅማቸዋል።
 7. የኢትዮጵያ ሕዝብ ተራርቆ መኖሩ ለዘመናት ከደረሰብት ድህነትና ስቃይ ተጨማሪ ኮሮና ቫይረስ እንዳይሆን ያለበትን ሁኔታ ለዕድገት እንጅ ለጥቃት እንዳይሆን እንዲጠቀምበት ከፍተኛ መነሳሳት ይደረግ።
 8. ይህንን ህብረተሰብ ያላቀፈ የዘላቂ ልማት ጥረት ብዙም ሊዘልቅ ስለማይችል አጋጣሚውን በመጠቀም የኮቪድን መከላከል ትምህርት ጋር ስለ ተሟላ ኑሮና እንዴት መደረስ እንደሚቻል የማስተማር እድሉ አሁን ነው።
 9. ለነዚህ ወገኖች ዋናው የጤና ማስጠበቂያና ለልማት ማሰማሪያ መንገድ እታች እንደተገለጸው ወደ ገጠር ዘመዶቻቸው በተመለሱት የከፍተኛ ትምህርት ተቅዋማት ተማሪዎችና መምህራን በኩል ቢሆን ብዙ አጥጋቢ ውጤት ያስገኛል።

፮፡ የሌሎች አገሮች አሰራርና ተመክሮ
፮-ሀ፡ በህንድ አገር የኬሪላ ግዛት ያደረጉት ስኬታማ የኮቪድ

የኬሪላ ግዛት 35 ሚሊዮን ህዝብ የሚገኝባት ክፍለ ሀገር ብዙ ቀውስ የሌለው፤ ርካሽና የተዋጣለት አሠሰራር በማካሄድ፤ የህዝብ ሥራ ተቅዋማትና ትምህርት ቤቶች ስያቋረጡ የተሻለ ውጤት አግኝተዋል። የአገሪቱ ዋና እንቅስቃሴ በአብዛኛው በግብርና ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ከዚህ በታች ለሂደታቸው መሳካት የረዱ ተግባራቶችን እንዳስሣለን።

 1. የመንግስት አሰራር፡ • ሁሉም የሚንስቴር መስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች የተስማሙበት ተስማሚ ፤ተመሳሳይ የሆነና የሚተጋገዝ እርምጃዎችን በመደንገግ ተገበሩ፤ • መንግስት 18 ኮሚቴዎችን አቋቁሞ በእየለቱ ህዝባዊ መግለጫዎችን በመስጠት ህዝቡን እያስተማረና ተግባሩን እያጠናከረ የህዝብን ጥያቄ እየመረመረ መፍትሄ ሰጠ • የሚያስተላልፏቸውም መመሪያዎችና መግለጫዎች ተመሳሳይና የማያደናግሩ ግልጽ በቀላሉ ህዝብ የሚረዳቸው ነበሩ
 2. ሁሉም ህብረተብ የተሳተፈበት • መንግስት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፎሎች ከባለሙያዎች ጋር በማወያየት የቫይረሱን ስርጭት ለማቆም ላካባቢ ተስማሚ እርምጃ በመውሰድ በማስፈጸም ስርጭቱን ተቆጣጠሩ
 3. ህዝብን ማስተባበር ማሳተፍ • ለህብረተሰቡ ስለ ህመሙ ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፍ። ህዝቡም ስለህመሙ ይዘት፤ ስለሚያስከትለው ስቃይና ጉዳቱ፤ ለመቆጣጠሬያ የወጡት መመሪያዎችን ተረድቶ በመተግበር ያለፍርሃት የዕለት ተግባሩን እንዲሰራ አደረጉ።
 4. ለሁሉም ህዝብ እንዲዳረስ ማንም ሰው ያለአገልግሎት እንድይቀር አደረጉ • አስፍለላጊ ቁሳቁሶችን እንደ መድሃኒት ምግብ ያሉትን ብህር በማጠራቀም የህዝብን በእተለይም ለአደጋ የሚጋለጡትን ፍላጎት ማሟላት ቻሉ።

፮-ለ፡ ከስዊድን የተገኙ ተመክሮዎች

 1. ስዊድን አውሮፓ ውስጥ ያደገና ህብረተሰቡን ተንከባክቦ የያዘ አስተዳደር ያለባት አገር ናት። ይህች 10 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት አገር ሃብታምና ለእያንዳንዱ ዜጋ የተሟላ አኗኗር ያሟላች አገር ናት። በህዝቡና በመንግስት መካከል ከፍተኛ መተማመንና አብሮ መስራት በአራያነት የሚጠቀስ አገር ነው።
 2. ስዊድን ኮቪድ-19ን ለመቆጣጠርና ስርጭቱን ለማቆም የወሰደችው እርምጃ ሊሎች የዓለም አገራት የተለየ ነው። እንደ ኬሪላ ህንድ ሥራዎችና ትምህርት ቤቶች ሳይተጓጎሉ የኮቪድን ጥቃት ለመቀነስ በሚደንቅ መንገድ ተግባሮችን አካሂደዋል።
 3. በመሆኑም በባቡርና በልዩልዩ መንገድ ከዓለም ጋር የተሳሰረችው አገር ከጎረቤቷ አግሮች ሲነጻፀር የደረሰባት ጉዳት የተሻለ ነበር። ይህ ሲሆን መስሪያ ቤቶችም ትምርት በቶችም ሳይዘጉ በመካሄዳቸው በሌሎች አገሮች የደረሰውን የኢኮኖሚ ድቀትና በህብረተስቡ የደረሰውን የኑሮ ጨንቀት ለመቋቋም እንደሚቻል አሳይተዋል።
 4. ይህ ሊሆንበት የቻለው ህዝቡ መንግስት የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሎ የሚተገብር፤ በአገር የመጣውን አደጋ ከመንግስት ጋር አብሮ ለመፍታት በመሰለፉ ነው። አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ እንደዘገበየችው ሁሉም ሰዎች የወረርሽኙን ወሬ እንደሰሙ የዕለት ተግባራቸውን በጥንቃቄ በማካሄድና በሰዎች መካከል መደረግ የሚገባውን እርቀት ጠብቀው በመኖር ውጤታቸው ከፍተኛ መሆኑ ነው።
 5. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደገ የመጣውን የኮቪድ ጥቃት ለመቀነስ የውጭ በሮቿን በጥብቅ መቆጣጠር አንዳንዶችን እስከ መዝጋት ደርሳለች።

፯፡ የኢትዮጵያ ወጣትን በሃላፊነት ማሰማራት

ከአብዛኛው የዓለም ወጣት ጋር ሲነፃጸር ከፍተኛ የትምህርት የደረሰው የኢትዮጵያ ወጣት ከልጅነት ጀምሮ ድህነትን የቀመሰ፤ በችግር ተፈትኖ ያደገ፤ ከጨቅላነት ጀምሮ እናትና አባትን በመርዳት ጠንክሮ መስራትን የለመደ ነው። እንደ በለጸጉት አገሮችም ወጣቶች ከህፃንነቱ ጀምሮ ገንቢ ትምህርት የመማር፤ በመጫዎቻዎች የመጫወት እድል ባያጋጥመውም ተጣጥሮ ለከፍተኛ ዕውቀት የበቃ፤ እንክብካቤ ከተደረገለት ለራሱ ለወገኑ ላገሩ ላዓለም ከፍተኛ አስተውጾ ሊያበረክት የሚችል ነው።
በኮቪድ-19 ምክንያት እያንዳንዱ ተማሪና መምህር ከዩንቨርስቲዎች ጋር ያለው ትሥስሩ ሳይቋረጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቆዩ የተደረገውን አጋጣሚ ለወጣቶች የብዙሃኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ችግርና ፍላጎት የመመርመሪያና ዘዴ የመፈለጊያ ላቦራቶሪ እንደገቡ የተደረገበት ጊዜ እንደሆነ ተደርጎ ቢወሰድ ከፍተኛ ወጤት ያመጣል።

እላይ እንደተጠቀሰው ከእያካባቢያቸው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር በቅድሚያ ስለኮቪድ-19 ያካባቢውን ቋንቋ ስለሚረዱ ህዝቡ በሚገባው መንገድ በማስተማር የወረርሽኙ ጉዳቱ ስይበዛ እንዲገታ በመርዳት ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረድ ይችላሉ።

በቀጣይም የህዝቡ አስቸኳይና ቀጣይ ችግሮችን በአንክሮ አይቶ ለመረዳትና እርምጃ ለመውሰድ፤ ከመሰሎቹ ጋርም በመወያየት መፍትሄ ማግኘት ላይ ይሯሯጣል። መቀንጨርን፤ የህፃናት ካምስት አመት እድሜ በፊት እንደ ቅጠል መርገፍን ለማቆም ይነሳሳል፤ የውሃ፤ የመብራት ሌሎችም ተፍላጊ አገልግሎቶችን አለመዳረስ ለመፍታት ዓይኑንና አዕምሮውን ይከፍታል፡ ፕሮጀኤክቶችም ተቀርጸው በስራ እንዲተገበሩ አስፈላጊውን አስተዋጾ ያደርጋል ያሳትፋል። ከፍተኛ ትምህርት አገርን ጠቃሚ በሆነ መንገድና ላገር ፍላጎት ማሟያ ትምህርት ለማስተማርና ተማሪዎች ትምህርት ሲጨርሱ ህብረተሰብን በሙያቸው ለማገልገል ብቃት ስለሚኖራቸው የስራአጥነት ጥላ ይገፋል። ይህም ማለት ወጣቱ ጊዜው የሚጠይቀውን ኢኖቬሽንና ዲጂታል ኢኮኖሚ ላገሪቷ ተስማሚ በሆነ መንገድ ተምሮ ማስፋፋት ይጠበቅበታል።


ይህን ዕድል እውን ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቅዋማትና የአገር አስተዳደር ክፍሎች ከአካባቢ የአስተዳደር ክፍሎች ጋር በመተባበር ወደታሰበው የልማት አቅጣጫ ሊያራምዱት ይችላሉ። በዚህም ዓይነት አገር ተደጋጋፊ ችግሮችን ባንድ ላይ በመፍታት እምርታ እድገት ታደርጋለች።

፰፡ ማጠቃለያ

የተውሶ ሄደ ተመልሶ፤ የሰው ወርቅ አያደምቅ እንደሚባለው፤ ለራስ በራስ ሰዎች የተሰራ የተከናወን ለክፉም ለደጉም ቀን የሚሆን አስተማማኝ እንደሆነ በዓለም የተመሰከረበት ጊዜ ነው። ለዘመናት ኢትዮጵያውያን መድሃኒት እየቀመሙ ወገንን አክመዋል፤ ብዙ የጥበብ የፈጠራ ነገሮችን አቅርበዋል፤ አያሌዎችንም የዓለም ህብረተሰብ እየተጠቀመባቸው ይገኛል። ለኢትዮጵያውያን መከላከያ፤ ለኢትዮጵያ ጥቅም ከራሳቸው ድሎት ቀንሰው የውጭ አገሮች ይደርሱልናል ብሎ ተግቶ ከመስራት መጠበቁ ቀርቶ ወደፊት ለህዝብ ለሀገር የሚሆናትን መፍጥሪያው አሁን ነው። እውነተኝው በክፉ ቀን ወይም ባደጋ ጊዜ ይፈተናል እንደሚባለው ኮቪድ-19ን መከላከል የምንችለው እኛው እራሳችን በማይጎዳንና በሚስማማን መንገድ መሆን አለበት።


የድሮ ኢትዮጵያውያን የአድዋ ጦርነትን ሲያሸንፉ የውጭ አጋዥ እንዳልነበራቸው ታሪክ ጸሃፊዎች ነግረውናል።እንዲያውም ይረዱናል ብለው የጠበቋቸ ወዳጅ የውጭ አገሮች ለምን ኢትዮጵያ የአውሮፓ አገርን አሸነፈች ብለው ቅሬታቸውን በስፋት እንዳቀረቡ የሚያሳዩ ሰነዶች አሉ። አሁንም ወገን በህብረትና በትጋት ህዝብን ከዳር እስከዳር በማሳተፍ ኮቪድ-19ን አልፈን ወደዘላቂ ልማት እናምራ። እዚህ ሰነድ ላይ እንደቀረበው በአገር በቀል ብልሃት፤ በህዝባዊ ህብረትና መረባረብ፤ በገጠር ለገጠሩ ተስማሚ በሆነ መንገድ፤ በከተማዎች የኢትዮጵያ አቅም በሚፈቅደው መሰረት፤ ወጣቱን ወደኃላፊነት በሚወስድ ተግባራዊ ትምህርት ላይ በማሰማራት የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገትን እንገእባ። ለሁሉም ህዝብ አንድም ሰው ሳይቀር የምትደርስ ኢትዮጵያን በማሳደግ፤ ለሁሉም የተሟላ ኑሮ መኖር ከዋስትና ጋር የምታስችል፤ ሰላምና ፍቅር የሰፈነባት፤ የበለፀገችና በዓለም ላይም ከፍተኛ ደረጃ እናድርሳት።

፱፡ ለግንዛቤ የሚረዱ ምንጮች

 1. Alipio, M. (2020). 2019-nCOV scare: 2019nCOV scare: Situation report, role of healthcare professionals and clinical findings. International Journal of Multidisciplinary Health Sciences Research, 8(9).
 2. GMCC, [2020] Handbook on COVID-19 Prevention and Treatment. https://covid-19.alibabacloud.com/
 3. አሕመድ, አቢይ፤ መደመር. አዲስ አባባ [2018] ISBN 978-99944-75-82-7
 4. ትእዛዙ, ባንትይሁን [2016] በመሓንዲሳው ዘዴ የተቃኘ ዘላቂ ልማት, ዘላቂ ልማትን በፍጥነት የሚያቀዳጅና ሰላምን የሚያሰፍን አሠራር. 4ኢፒአር ኢንተርፕራይዝ, ቶሮንቶ ISBN 978-0-9949938-1-6
 5. Kinfe Gebeyebu (2013). History of Epidemics in Ethiopia. In: The Manual of Ethiopian Medical History. Enawgaw Mehari, Kinfe Gebeyehu, Zergabachew Asfaw (Eds). [2012] People to People, Inc, USA ISBN: 978-0-9891322-0-6, pp 35-43.
 6. Richard Pankhurst (1990). An Introduction to the Medical History of Ethiopia. Red Sea, New Jersey, USA, pp 15-70. 7
 7. How Kerala is managing the COVID-19 pandemic: website references https://www.newframe.com/kerala-is-a-model-state-in-the-covid-19-fight/ https://www.asianage.com/opinion/columnists/060420/covid-19-how-kerala-has-shown-us-the-way.html https://www.government.se/government-policy/the-governments-work-in-response-to-the-virus-responsible-for-covid-19/
 8. How Sweden is managing COVID-19 pandemic: website reference https://www.government.se/articles/2020/04/strategy-in-response-to-the-covid-19-pandemic/
 9. Reguera, J., et. al., [2014]. A structural View of coronavirus-receptor interactions, Virus Res, http://dx.doi.org/10.1016/j.virusres.2014.10.005
 10. Kam, K., et al., [2020]. A Well Infant with Coronavirus Disease 2019 (Covid-19) With High Viral Load. Oxford University Press for the Infectious Diseases Society of America
 11. Li, W., et al., [2006]. Animal Origins of the Severe Acute Respiratory Syndrome Coronavirus: Insight from ACE2–S-Protein Interactions. Journal of Virology, May 2006, p. 4211–4219
 12. L’Her, E., [2011]. Bench Tests of Simple, Handy Ventilators for Pandemics: Performance, Autonomy, and Ergonomy. RESPIRATORY CARE • JUNE 2011 VOL 56 NO 6
 13. Somily, A., BaHamma, A. [2020]. Coronavirus Disease‑19 (Severe Acute Respiratory Syndrome‑Coronavirus‑2) is not Just Simple Influenza: What have we Learned so Far. Journal of Nature and Science of Medicine ¦ Volume XX ¦ Issue XX IP: 10.232.74.26 http://www.jnsmonline.org
 14. Aaltol, M., [2020]. Covid-19 – A Trigger for Global Transformation? Political Distancing, Global Decoupling and Growing Distrust in Health Governance. FIIA Working Paper, ISBN 978-951-769-632-6 ISSN 2242-0444
 15. Ton, T. [2009]. Drug Targets in Severe Acute Respiratory Syndrome (SARS) Virus and other Coronavirus Infections. Infectious Disorders – Drug Targets 2009, Vol. 9, No. 2
 16. Rao, K., et al., [2020]. Review on Newly Identified Coronavirus and its Genomic Organization. SSR Inst. Int. J. Life Sci. ISSN (O): 2581-8740 | ISSN (P): 2581-8732
 17. Corman, V., et. al., [2014]. Rooting the Phylogenetic Tree of Middle East Respiratory Syndrome Coronavirus by Characterization of a Conspecific Virus from an African Bat. Journal of Virology Vol. 88(19):11297. DOI: 10.1128/JVI.01498-14.
 18. Lu X, Zhang L, Du H, et al. SARS-CoV-2 infection in children. N Engl J Med. DOI: 10.1056/ NEJMc2005073
 19. Garfin, R., et., al. [2020] The Novel Coronavirus (COVID-2019) Outbreak: Amplification of Public Health Consequences by Media Exposure. American Psychological Association 2020, Vol. 3, No. 999, 000 ISSN: 0278-6133 http://dx.doi.org/10.1037/hea0000875
 20. Andersen, K., et. al., [2020]. The proximal origin of SARS-CoV-2. Nature Medicine, https://doi.org/10.1038/s41591-020-0820-9
 21. Perkins, J. Confessions of an Economic Hitman. Berrett, Koller San Fran 2004
 22. Taleb, Nassim The Black Swan, The Impact of the Highly Improbable. Random House [2007]
 23. Christensen, Clayton, et. al. The Prosperity Paradox. How Innovation Can Lift Nations Out of Poverty.